TM Law Firm Accessibility
×

መዝገቡ የቀረበው: ለፌዴራል ግብር ይግባኝ ኮሚሽን
ጉዳዩ ፣ የህክምና መሳሪያዎች የቀረጥ ዋጋ በሕግ አግባብ አልተተመነልኝም የሚል ነው
ይግባኝ ባይ፡ ቲ ኤም የጥብቅና እና የህግ ምክር አገልግሎት ድርጅት ስለ አለም ኢንተርናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማህበር
መልስ ሰጭ፡ ጉምሩክ ባለስልጣን


የይግባኝ ባይ የቅሬታ ነጥቦች ይግባኝ ባይ አለም ኢንተርናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማህበር ከውጭ ሀገር የህክምና መሳሪያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ለእነዚህ መሳሪያዎች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ እ.ኤ.አ. በ2025 በጉምሩክ በኩል ያስገባበትን የግብይት ዋጋ 2200፣7300፣10000፣700፣560፣ እና 900 በገዛበት ዋጋ ለመሆኑ ማሰረጃ አቅርቦ ቀረጥ ለመክፈል ሲጠይቅ መልስ ሰጪ ግን ይግባኝ ባይ ያቀረበውን ዋጋ ከራሱ ከጉምሩክ የዋጋ መረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) ጋር በማነጻጸር ከአምስት በመቶ(5%) በላይ አንሷል በማለት ውድቅ አደረገው። ከዚያም ምክንያት በመልስ ሰጭ በዳታ ቤዝ ባለው ዋጋ ለእያንዳንዱ ለገባው እቃ 3100፣9500፣11586፣1830፣1250፣2350 መሠረት ቀረጥና ታክስ በይግባኝ ባይ ላይ ወሰነ። ይግባኝ ባይ ይህን የመልስ ሰጭን ውሳኔ በመቃወም ጉዳዩን ለግብር ይግባኝ ኮሚሽን አቤቱታ ድርጅታችን አንዲያቀርባላቸው ጠይቀው ጉዳዩ ክርክር ከተደረገባት በኃላ የሚከተለውን ውሳኔ አግኝቶአል።


የድርጅታችን አለማ

ይግባኝ ባይ በገዛበት ትክክለኛውን ዋጋ እንዲከፍል እንጂ በዳታ ቤዝ ውስጥ ባሉ ሌሎች ይግባኝ ባይ ካስመጣቸው እቃዎች ጋር ያልተመሳሰሉ መሳሪያዎች መሰረት ተደርጎ ዋጋ እንዳይገመት ማድረግ ዋነኛው አላማ ነው።


በክርክር የተነሱ ዋና ዋና የይግባኝ ባይ ነጥቦች

 ይግባኝ ባይ ያስገባቸው የህክምና መሳሪያዎች ከሸንዚን ኮመን ሜዲካል ኢንቨትመንትስ ኩባንያ (Shenzhen comen instrument medical company limited) ከተባለ አምራች ድርጅት በአግባቡ የተገዙ ናቸው፡፡

 ይህ አምራች ድርጅት የዕቃዎቹን የዋጋ ዝርዝር በኢሜል እና በዲኤችኤል አማካኝነት ለመልስ ሰጪ ልኳል። ይህ የዋጋ ዝርዝር ይግባኝ ባይ ያስገባቸውን እቃዎች ስያሜ፣ መጠን እና መለዋወጫዎች በዝርዝር ይገልጻል፡፡

 መልስ ሰጪ የይግባኝ ባይ ያቀረበውን ማስረጃ በአግባቡ አለመመርመሩ ማስረጃ ምዘና ላይ ያለውን ክፍተት አሳይቶአል፡፡

 በዚህም ሳቢያ የመልስ ሰጭ አቤቱታ አጣሪ ዳይሬክቶሬት የዋጋ ዝርዝሩን ሳይመረምር እና በተመሳሳይ ስያሜ ለሚታወቁ እቃዎች የተለያየ ዋጋ መኖሩን በማንሳት ውድቅ ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑን ፣


በመልስ ሰጪ የቀረበ መልስ ዋና ዋና ነጥቦች

 ይግባኝ ባይ ያቀረበው ዋጋ ከዳታ ቤዝ ጋር ሲነጻጸር ከአምስት በመቶ በላይ ልዩነት ስለነበረው ውድቅ ማድረጋችን ሕጋዊ ነው ሲል ተከራክሯል። በተጨማሪም ይግባኝ ባይ ያቀረበው የአምራች የዋጋ ዝርዝር ሲመረመር አምራቹ ለሌሎች አስመጪዎች ለተመሳሳይ እቃዎች የተለያየ ዋጋ መስጠቱ አረጋግጫለው ። ለምሳሌ አንድ አይነት የህክምና መሳሪያ ለአንድ አስመጪ 150 ዶላር ፣ ለሌላ አስመጪ ደግሞ 2100 ዶላር መሰጠቱን አንስቷል። ይህ ልዩነት በዋጋ ዝርዝሩ ላይ ከተጠቀሰው እስከ አስራ አምስት በመቶ ልዩነት እጅግ የላቀ በመሆኑ በይግባኝ ባይ የቀረበው መረጃ ተአማኝነት የጎደለው ነው።

 የህክምና መሳሪያዎቹ ተመሳሳይ ስም ቢኖራቸውም በመጠናቸው፣ አብሮ በሚመጡ መለዋወጫዎች አይነት፣ ብዛት እና ጥራት ልዩነት ስላላቸው ዋጋቸው ሊለያይ ይችላል። በዋጋ ዝርዝሩ ላይ እንኳን በተጨማሪ መለዋወጫዎች ላይ በመመስረት ዋጋ እስከ አስራ አምስት በመቶ (15%) ሊለያይ ይችላል ። ይህ ማለት ተመሳሳይ መሳሪያዎች እንኳን በመለዋወጫቸው ምክንያት የተለያየ ዋጋ ሊኖራቸው እንደሚችል በግልጽ ያሳያል፡፡


የይግባኝ ኮሚሽኑ ውሳኔ ዋና ነጥብ

በዚህም ኮሚሽኑ ይግባኝ ባይ ያቀረበው የዋጋ ዝርዝር በወቅቱ ባለው የገበያ ሁኔታ መሰረት መስፈርቱን ያሟላ መሆኑን እና በተጨማሪም የመልስ ሰጪ የአስተዳደራዊ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ ነው ብሎ መደምደም አለመቻሉን ገልጿል። ኮሚሽኑ መልስ ሰጪ ያቀረበውን የዳታ ቤዝ ዋጋ ብቻ በመውሰድ ውሳኔ መስጠት በቂ አለመሆኑን እና የአምራች የዋጋ ዝርዝር መመርመር እንዳለበት ግልጽ አድርጓል። በተጨማሪም አንድ መቶ ሃምሳ አምስት ዶላር ዋጋ በምን አይነት መለዋወጫዎች እንደተሰጠ ባለመገለጹ ትክክለኛነቱ አልተረጋገጠም ።


ለውሳኔው መሰረት የሆኑ ዋነኛ የከርክር ነጥቦች

 ከአምራች ድርጅት የተላከ የዋጋ ዝርዝር መልስ ሰጭ አለመመርመሩ፣

 በመልስ ሰጪ ለማነጻጸሪያነት የተጠቀመበት የአንድ መቶ ሃምሳ አምስት ዶላር ዋጋ ትክክለኛነት አለመረጋገጡን ፣

 መሳሪያዎቹ ተመሳሳይ ስም ቢኖራቸውም በመለዋወጫዎች ምክንያት የህክምና መሳሪያዎች ዋጋ እንደሚለያይ የግባኝ ባይ ማስረዳት መቻሉ፣

 ይግባኝ ባይ ለመልስ ሰጭ ቀረጥ ለመክፈል ያቀረበውን የዋጋ ዝርዝር በመልስ ሰጪ በአግባቡ ሳይመረምር ውድቅ ማድረጉን ስህተት መሆኑን ኮሚሽኑ ማረጋገጡ ናቸው፡፡


በመጨረሻም የግብር ይግባኝ ኮሚሽን የመልስ ሰጪ የአስተዳደር ውሳኔ በመሻር ጉዳዩ እንደገና የግባኝ ባይ ያቀረበው የህክምና መሳሪያዎቹ ትክክለኛ ዋጋ በአግባቡ እንዲያጣራ አዘዘ። ማለትም ደንበኛችን ይግባኝ ባይ ያቀረበው የዋጋ ዝርዝር እና ማስረጃዎች መሰረት በማድረግ ተጣርቶ ቀረጥ እንዲከፍል ተወስኖለታል።